Search
  • Bekele Shanko

ለኢትዮጵያ ዘለቄታዊ ሰላምና እድገት

Updated: Jul 24, 2018


ለኢትዮጵያ ዘለቄታዊ ሰላምና እድገት ትኩረት የሚሹ ሰባት ነጥቦች
ለኢትዮጵያ ዘለቄታዊ ሰላምና እድገት ትኩረት የሚሹ ሰባት ነጥቦች

ሰላምን፥ በአንድነት መኖርንና የመናገር ነጻነትን ተጠምተን የኖርን እኛ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ባለፉት ሦስት ወራት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አመራር ሕልም የምናይ እስኪመስለን ድረስ ልባችንን የሚያረኩ ሥራዎች ሲሠሩ አይተናል። መላውን የአገሪቱን ክፍል እያነቃነቀና ዓለምን እያነጋገረ ባለው የከፍተኛ የለውጥ ንቅናቄ ውስጥ እያለፍን ባለንበት በዚህ ጊዜ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ብዬ የማምናቸውን ሰባት ነጥቦች ከዚህ ቀጥሎ አቀርባለሁ።

እነዚህን ነጥቦች ስሰጥ ከአገር ውጭ ስለምኖርና በኢትዮጵያ ያለውን ሁሉ በቅርብ ስለማላውቅ ሁኔታዎችን የማይበት መነጽር ትክክለኛ ላይሆን ይችላል። ቢሆንም ግን እንደ ኢትዮጵያዊነቴ ለጠቅላይ ሚኒስትራችን፥ አብረዋቸው ለሚሠሩ ባለሥልጣናትና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይጠቅማል ብዬ ስለማምን የበኩሌን አስተጽኦ ላድርግ ብዬ ነው።


1. ለማስፈጸም የሚያስችል በቂ አቅም ሳይኖር ብዙ ፕሮጀክቶችን በአንድ ጊዜ መጀመር ጥሩ አይደለም።


ለዘመናት አብረውን የኖሩ ውስብስብና ፈርጀ ብዙ ችግሮቻችን በአንድ ቀን፥ በአንድ ወር ወይም በአንድ ዓመት ሊወገዱ አይችሉም። መወገድ ቢችሉ እንዴት ደስ ባለኝ! ነገር ግን ከሩቅ ሆኜ ሳይ ዶ/ር አብይ ባለፉት ሦስት ወራት እጅግ ብዙ የሆኑ ፕሮጀክቶችን ጀምረዋል።

ጥያቄዬ ግን እነዚህን ፕሮጀክቶች ተከታትሎ የማስፈጸም አቅም ያላቸውና ታማኝ የሆኑ ብዙ ሰዎች በአጠገባቸው አሉ ወይ?


2. ቅድሚያ ለሚገባቸው ነገሮች ቅድሚያ መስጠት


ዶ/ር አብይ በዚህ ጊዜ ቅድሚያ ሊሰጡ ከሚገባቸው ነገሮች አንዱ በሕዝብ መካከል እየተፈጠረ ያለውን አለመረጋገት ማብረድና ማጥፋት ነው። ለምሳሌ ያህል ከሲዳማ፥ ከወላይታ፥ ከቤኒሻንጉል፥ ወዘተ የአገር ሽማግሌዎች፥ የመንግሥት ባለሥልጣናት፥ የሃይማኖት መሪዎችና የጸጥታ ኃይላት ጋር በመነጋገር ሕዝብን ከሕዝብ ጋር የሚያጋጩ ኃይላት አቅም እንዳይኖራቸው ማድረግ ነው።

ሌላው ቅድሚያ ሊሰጡት የሚገባቸው ነገር በአጠገባቸው ያሉትን መሪዎች ማንነታቸውን በሚገባ ማወቅ፥ የኢትዮጵያን አንድነትና አድገት በሚመለከት እርሳቸው የሚያዩትን ራእይ እነርሱም በትክክል እንዲያዩ ማስቻልና ማደራጀት ነው ብዬ አምናለሁ። እንደ እነዚህ ዓይነቶቹ ሰዎች በአጠገባቸው በበቂ ሁኔታ ከሌሉ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ቅድሚያ ሰጥተው ታማኝ የሆኑ መሪዎችን መመልመል፥ ከመሪዎቹም ጋር በቂ ጊዜ መውሰድ፥ እና ግልጽ የሆነ ኃላፊነትን መስጠት ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ።


3. ትክክለኛ መሪዎችን በትክክለኛው ቦታ መመደብ


ይህ ያለንበት ጊዜ በምድራችን ላይ ትልቅ የሆነ የአንድነት፥ የሰላምና የልማት ተስፋ የሚታይበት ጊዜ ነው። በዚህ ጊዜ ራዕዩ እንዳይጨናገፍ ባለሥልጣናት ሲመደቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው። ሰዎችን መሾም ቀላል ነው፥ መሻር ግን ብዙ ዋጋ ያስከፍላል። የአመራር ቦታ ክፍት እንዳይሆን ተብሎ በባሕርያቸውና በብቃታቸው ያልተፈተሹ ሰዎችን በመሪነት ማስቀመጥ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል። ብቃት ያላቸው፥ታማኝ የሆኑና የጠቅላይ ሚኒስትሩንና የኢትዮጵያን ሕዝብ ራእይ የሚጋሩ እውነተኛ መሪዎች እስከሚገኙ ድረስ ለጥቂት ሳምንታት ወይም ወራት በተጠባባቂ መሪዎች ቦታ አስይዞ መጠበቅ ይሻላል።


4. እኛ የለውጡ ተጠቃሚዎች ደግሞ በሶሻል ሚዲያዎች የማይረቡና አፍራሽ የሆኑ ነገሮችን ከመጻፍ መቆጠብ።


ባገኘነው የመናገር ነጻነት እጅግ ደስ ብሎኛል። ነገር ግን ምን እንደምንጽፍ፥ ምን እንደምንናገር እና ለምን ዓላማ እንደምናንገር ማወቅ ያስፈልጋል። በዚህ ጊዜ መናገርና መጻፍ ያለብን ስለ አንድነት፥ ስለ እድገት ራእይ፥ አዳዲስ ሥራዎችን ስለ መፍጠር፥ ድህነትን ስለማሸነፈ፥ በዓለም ዙሪያ የተነቀፈውን ስማችንን ስለማደስ፥ መልካም ሆኖና መልካም ሠርቶ ለመታወቅ እንጂ መሳደብ፥ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር የሚከፋፍሉና የሚያጋጩ ነገሮችን መጻፍ አያስፈልግም። ንግግራችን የበሰለና ሚዛኑን የጠበቀ መሆን አለበት።


5. የኢትዮጵያ ጠላቶች በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆኑ በውጭም እንዳሉ ማወቅ


በዚህ ግርግር በበዛበት ጊዜ በተለያዩ ምክንያቶች ከውጭ አገር የሚገቡ ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ ሰዎች ድብቅ ተልእኮ ሊኖራቸው ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ ያሰፈልጋል። የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነትና ልማት የማይወዱ ግለሰቦች፥ ቡድኖችና አገሮችም ሊኖሩ ይችላሉ። ስለዚህም ጥንቃቄ በጎደለ ሁኔታ ጓዳችንን ማሳየት አያስፈልግም። ዶ/ር አብይም ከማን ጋር እንደሚገናኙ፥ ምን እንደሚበሉ፥ ምን እንደሚጠጡ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።


6. የቀደሙ መሪዎችን በጅምላ ክፉ ናቸው ማለት ትክክል አይደለም


ያለፉትን አመራር መውቀስ ብቻ ስይሆን ካለፈው መማር፥ መልካም የሆነውን መጠቀም እና ደካማ ጎኖችን ማረምና ማስወገድ እጅግ አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ ያህል ብዙ ጊዜ በአፍሪካ የሚታዩ ችግሮች ከቀደሙት መሪዎችና ሥርዓቶች ለመማር ያለን ፍላጎት ደካማ መሆኑ ነው። ሁሉን አፍርሰን አዲስ መጀመር ሳይሆን መልካሙን መርጠን፥ ክፉውን ጥለን ካለፈው የተሻለ ሥራ መሥራት ቀጣይነት ላለው እድገት አስፈላጊ ነው።

ያለፈውን አመራር መውቀስና መልካም ያልሆነውን ብቻ ማግነን ትክክል አይደለም። ማንኛውም የሰው አመራር ፍጹም አይደለም። ለምሳሌ ያህል በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር በአቶ መለስ አመራር ጊዜ የተፈጠሩ ስህተቶችን ብቻ መቁጠር ለእድገት አይጠቅምም። ድካም ብቻ ብንፈልግ በመቶ የሚቆጠሩ ድካሞችን መዘርዘር እንችላለን። ብዙ ድካሞችና ስህተቶች እንደነበሩ ሁሉ ብዙ መልካም ነገሮችም እንደተሠሩ መርሳት የለብንም።

ለምሳሌ ያህሌ በአቶ መለስ ጊዜ የተፈጸሙ ዋና ዋና ስህተቶችን ለመጥቀስ ያክል የባንዲራችን ጉዳይ፥ የባሕር በር ማሳጣት፥ ከኤርትራ ሕዝብ ጋራ ማጣላት፥ ሕዝብን በሚከፋፍልና የአገርን አንድነት በሚበታትን ሁኔታ ብሔርንና ቋንቋን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ አደረጃጀት፥ በተለያዩ ምክንያቶች ከአገር እየተሰደዱ በየበረሃው፥ በየጫካው፥ በባሕርና በውቅያኖስ እየተበሉ ለሚጠፉ ኢትዮጵያውያን ትኩረት አለመስጠት፥ ዘረኝነት፥ እና ሙስና የመሳሰሉ ችግሮች በምድራችን ሲስፋፉ አይቶ ዝም ማለት።

በአንጻሩ ግን በአቶ መለስ ዘመነ መንግሥት ከተሠሩ ብዙ መልካም ሥራዎች መካከል ጥቂቱን ለመጥቀስ ያክል ጥራቱ ዝቅተኛ ቢሆንም የከፍተኛ ትምህርት በአገሪቱ መስፋፋት፥ የአገርን ኢኮኖሚ የማሳደግ ራእይ፥ የመንገዶችና የሕንጻዎች መስፋፋት፥ የባቡር መንገዶች መዘርጋት፥ ለአፍሪካ ሕዝቦች ልማት የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረግ የሚጠቀሱ ናቸው ብዬ አምናለሁ።

በዚህም ምክንያት ነው አቶ መለስ በሞቱ ጊዜ ብዙዎቻችን እንባ ያፈሰስነው። መልካሙን እየፈለግን ያለፈውን ማመስገን ካልቻልን ከእኛስ በኋላ የሚመጡት እኛ የሠራነውን መልካም ሥራ እንዴት ማመስገን ይችላሉ?


7. ዶ/ር አብይንና አብረዋቸው ለኢትዮጵያ አንድነትና እድገት ለመሥራት የቆሙትን ሁሉ መውደድና መደገፍ።


እግዚአብሔር የብዙ ዘመን ጸሎታችንን ሰምቶ፥ በምድራችን የፈሰስውን የብዙ ንጹሃን ዜጎችን ደም ተመልክቶ፥ ዶ/ር አብይንና ከእርሳቸው ጋር ለኢትዮጵያ ሰላምና እድገት ለመሥራት የተነሱትን መሪዎች ላከልን። ስለዚህም ክብሩን ለእግዚአብሔርን ልንሰጥ ይገባል።


ዶ/ር አብይም በትህትና፥ በማስተዋልና በጥበብ አሁን የጀመሩትን ራእይ አሳድገው የኢትዮጵያን ሕዝብ እንዲመሩ፥ እንዲሁም እግዚአብሔር ለአካባቢ አገሮችና ለዓለም ሁሉ መልካም ምሳሌ እንዲያደርገን ጸሎቴና ምኞቴ ነው። እግዚአብሔር የሰጠንን መሪዎች ከክፉ ይጠብቅ፥ ኢትዮጵያን ይባርክ፥ ለብዙዎችም በረከት ያድርገን።

4 views0 comments