Search
  • Bekele Shanko

ኢትዮጵያ የአጭርና የረጅም ጊዜ ተግዳሮቶችዋን እንዴት ማስወገድ ትችላለች? ክፍል ሁለት

በዚህ ርዕስ ስር ከሁለት ሳምንት በፊት ክፍል አንድን ማቅረቤ ይታወሳል። በዚያም ጽሑፌ ኢትዮጵያ የአጭርና የረጅም ጊዜ ተግዳሮቶችዋን እንዴት ማስወገድ ትችላለች ለሚለው ጥያቄ መልስ የሚሆኑ ሦስት ነጥቦችን አንስቼ ነበር። ነጥቦቹንም ለማስታወስ ያክል (1) ከሁሉ አስቀድሞ በአገሪቱ ሰላምን ማስፈን፥ (2) ወቅታዊ ችግሮችን እንደ ዕድል መጠቀምና ለችግሮቹም የረጅም ጊዜ መፍትሄዎችን መፈለግ፥ እና (3) ከማውራት ይልቅ መሥራት የሚሉ ነበሩ። ዛሬ ደግሞ ተጨማሪ ሦስት ነጥቦችና ልስጣችሁ።


4. ለሕዝብና ለአገር እድገት የሚጠቅሙ ሕጎችን ማውጣትና ለሕጎቹም መገዛት


በአገራችን እስከዛሬ የጸደቁና በሥራ ላይ የዋሉ ሕጎች በአብዛኛው የገዢውን መደብ ፍላጎት ያንጸባረቁ ናቸው ብል ማጋነን አይሆንም። የአንድ አገር ሕግ የአንድን ፖለቲካ ፓርቲ አመለካከት ለማንጸባረቅ ወይም የገዢውን መደብ ፈቃድ ለማስፈጸም የሚዘጋጅ ከሆነ፥ የሚመራው አካል በተቀየረ ቁጥር ሕጉም ይቀየራል ማለት ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ አገር መሠረት የላትም።


በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ውስጥ ብዙ የሚሻሻሉ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ ያህል ብሔርንና ቋንቋን መሰረት ያደረገው፥ እንዲሁም መገነጣጠልን የሚያበረታታው የፖለቲካ ፍልስፍና ጊዜ ሳይሰጠው መለወጥ ያለበት ሕግ ነው። ሕጋችን ሲሻሻል ግን በቅርብ ጊዜ እይታ የተወሰነ መሆን የለበትም፤ ነገር ግን መሰረታዊና ትውልድ ተሸጋጋሪ መሆን አለበት።


ሕግ አንዴ ከወጣና ከጸደቀ በኋላ ደግሞ የአገሪቱ ዜጋ ሁሉ ለሕጉ መገዛት ይኖርበታል። ማንም ከሕግ በላይ ሊሆን አይችልም። ነገር ግን የምድራችን ትልቅ ችግር ምንድር ነው ብላችሁ ብትጠይቁኝ ለሕግ አለመገዛት ነው። በአገራችን ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ ለሕግ የሚታዘዘው ድሃውና ተከታዩ ሕዝብ እንጂ ሀብታሙና መሪው አይደለም። “ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ” እንደተባለው ገንዘብ ያለው ከሕግ በላይ ሲኖር ተመልክተናል። እንዲሁም “ጢስና ደፋር መውጫ አያጣም” እንደተባለው የፖለቲካ ሥልጣን ያለው ደግሞ ሕግን ጥሶ የፈለገውን ሲያደርግ አይተናል።


በምድራችን የሕግ የበላይነት ከተከበረ ሥልጣኑን ያለአግባብ የሚጠቀም ባለሥልጣን በሕግ ተጠያቂ ይሆናል፤ በሙስና የተያዘ ብቻ ሳይሆን የተጠረጠረም ቢሆን ወደ ሕግ ፊት ይቀርባል፤ ሲዋሽ ወይም ሲያጭበረብር የተገኘ ሰው በሕግ ይጠየቃል። ነገር ግን እነዚህንና ተመሳሳይ በደሎችን የሚፈጽሙ ሰዎች አብዛኞቹ ባለሥልጣናት በመሆናቸውና ከሕግ በላይ የሆኑ ስለሚመስላቸው ሕግን ለማስከበር የሚያስችል የሞራል ጉልበት አይኖራቸውም። ከዚህ የተነሣ አገሪቷ ሕግ እያላት ያለ ሕግ ትኖራለች ማለት ነው።


ለምሳሌ ያህል አሜሪካን አገር አንድ ሰው ጥፋት ቢያጠፋ፥ ጥፋቱ በኮምፒዩተር ስለሚመዘገብ ሥራ ፈልጎ የማግኘት ዕድሉ የመነመነ ነው። የትም ከተማ ቢሄድ ስሙንና የመታወቂያ ቁጥሩን ከተናገረ ጥፋቱም አብሮ ብቅ ይላል። ይህም እንዳይሆን እያንዳንዱ ሰው ጥፋት እንዳይገኝበት ተጠንቅቆ እና ሕግን አክብሮ ይኖራል።

በአንድ አገር ውስጥ ውስጥ ሕግን የሚያስጠብቀውና ጸጥታን የሚያስከብረው አካል ሕግን የሚያፈርስ ከሆነ አገሩ ሕገወጥ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚና በማሕበራዊ ሕይወቱ የማደግ አቅሙ እጅግ ደካማ ነው።


ለምሳሌ ያህል ከጥቂት ዓመታት በፊት ለሥራ ጉዳይ ኢትዮጵያ ገብቼ፥ ባልንጀራዬ መኪና እያሽከረከረ እናቴን ለመጠየቅ ወደ ገጠር ስንሄድ የትራፊክ ፖሊስ በመንገድ ላይ አስቆመን። ከዚያም የነጂውን መንጃ ፈቃድ ጠይቆ ወሰደ። ለቤተሰቤ ስጦታ የሚሆን ልብስ፥ ጨው፥ ዳቦ፥ ስኳርና ሳሙና ይዘናል። ከዚያም ፖሊሱ መንጃ ፈቃዱን አልመልስም አለ። ምክንያቱ ምንድር ነው ብዬ ባልንጀራይን ስጠይቅ ጉቦ ፈልጎ ነው አለኝ። እኔም “ለምንድር ነው ያስቆምከን? ወንጀላችንስ ምንድር ነው? መንጀ ፈቃዱንስ ለምንድር ነው የማትመልሰው?” ብዬ ስጠይቀው በቁጣ “የፈለግሁትን ለማድረግ ሥልጣን እንዳለኝ ታውቃለህን?” አለኝ። ሕግን ለማስከበር ሥልጣን የተሰጠው ሰው ሕግ ሲጥስ ማለት ይሄ ነው። ብዙ ካጉላላን በኋላ፥ ጉቦ ለመስጠት ፈቃደኞች አለመሆናችንን ሲያውቅ፥ መንጀ ፈቃዱን ሰጥቶን፥ አንጀቴ እየተቃጠለና አገሬ ኢትዮጵያ የምትለወጥበትን ቀን እየናፈቅኩ መንገዳችንን ቀጠልን።


5. የሚሠሩ ሥራዎችን በእቅድ መሥራት


አብዛኞቹ በአገራችን የሚሠሩ ሥራዎች በራእይ፥ በእቅድና በቅንጅት ሲሠሩ አናያቸውም። ለምሳሌ ያህል አንድ የአስፋልት መንገድ ተሠርቶ ሳያልቅ መፍረስ ይጀምራል። በአሥር ዓመት ውስጥ የሚፈርስ መቶ ኪሎ ሜትር መንገድ ከመሥራት ይልቅ መቶ ዓመት የሚቆይ አሥር ኪሎ ሜትር መሥራት ይሻላል። ገንዘብ መውጣቱ ካልቀረ ለምን ጥራት ያለውን ሥራ አንሠራም?


በተጨማሪም ባለፉት ዓመታት ውስጥ በአዲስ አበባ ከተማ ብዙ የኮንደሚኒየም ቤቶች ተሠርተዋል። እነዚህ ቤቶች ግን ከተማውን ለማሳደግ ካለው ወይም ሊኖር ከሚገባው ራእይ ጋር ተመጣጣኝነት የሌላቸው ናቸው። ማለትም የአዲስ አበባ ኮንደሚኒየም ቤቶች ምናልባትም የዛሬ አሥር ወይም አሥራ አምስት ዓመት “ከተማውን ስላቆሸሹ መፍረስ አለባቸው” ሊባሉ የሚችሉ ናቸው። እነዚህ ቤቶች በረጅም ጊዜ ራእይ የተሠሩ ባለመሆናቸው የነገው እሴት ሳይሆኑ እዳ ናቸው።


በተመሳሳይ ሁኔታም የአዲስ አበባን ከተማ ዕድገት ስናይ የሚያስደስቱ ነገሮች እንደ መኖራቸው ሁሉ የሚያሳዝኑ ነገሮችም አሉ። አዲስ አበባ ንጹህ ያልሆነ እና መጽዳት የሚገባው ከተማ እንደሆነ እናውቃለን። ታዲያ ድሮ የተሠራውን እያጸዳን አዲስ የሚሠራውንስ ለምን በዘመናዊ መንገድ አንሠራውም? የድሮ ይዞታ ጽዳት የሚያስፈልገው ከሆነ፥ አዲስ የሚስፋፋውም አካባቢ ከድሮው የማይሻል ከሆነ፥ ገንዘባችን በማጽዳት (በማፍረስና በመገንባት) አለቀ ማለት ነው።


ስለዚህ የድሮውን እያስተካከልን፥ አዲሱን ግን ደረጃውን በጠበቀ እና በዘመናዊ አሠራር ልንገነባ ያስፈልጋል። የከተማ ልማት የሚመሩ ሰዎች ለምን ወደ ደቡብ ኮሪያ፥ ሲንጋፖር፥ ካናዳ የመሳሰሉትን አገሮች ሄደው ትምህርታዊ ጉብኝት አያደርጉም? ያዩትንና የተማሩትንስ ለምን በሥራ ላይ አያውሉትም? የገንዘብ አቅማችን በጣም አነስተኛ እንደሆነ አውቃለሁ። ነገር ግን እድገት ከጥቂት ይጀምራል። ባለን አቅም፥ ትንሽም ቢሆን ሥራችንን ዕቅድና ጥራት ባለው ሁኔታ መሥራት ያስፈልጋል። ከተማው ውስጥ ሕንጻዎች ሲሰሩ ዛፎች መትከል፥ አካባቢውን አረንጓዴ ማድረግ እና በቂ የመኪና ማቆሚያ መዘጋጀት አለበት። ለወደፊትም መንገድ ለማስፋት የሚያስችል ሰፊ ቦታ ከሕንጻው ፊት ለፊት መኖሩ ተገቢ ነው። ቴሌ ቆፍሮ ከከደነ በኋላ የውኃ ሥራዎች ወይም የኤሌክትሪክ ባለሥልጣን ደግሞ የሚቆፍረውን ማንሳት አያስፈልግም፤ በቂ ምሳሌ ሰጥቼአለሁና።


6. ከመሰዳደብና ከመጣላት ይልቅ መከራከርና መማማር


ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም በሶሻል ሚዲያዎች ላይ ሰዎች የሚጽፉአቸውን ነገሮች አልፎ የማየት ዕድል አግኝቻለሁ። የሚጠቅምም የሚጎዳም ነገር አለ። በተለይ መሰዳደብ፥ መከፋፈልና መጣላት ሁሉን ይጎዳል፥ ማንንም አይጠቅምም። የመሰዳደብና የመገዳደል ፖለቲካ ወይም ማኀበራዊ ግንኙነት እጅግ ኋላ ቀር ነው። ዛሬ ያደጉ አገሮች ጸሐይ ወዳለችበት እንድረስ፥ ጨረቃ ለእርሻ ተስማሚ እንደሆነ ጥናት እናድርግ፥ ለወታደሮቻችንን መኖሪያ በአየር ላይ ወይም በታችኛው ሰማይ ውስጥ እንሥራ እያሉ ባሉበት በዚህ ጊዜ እኛ ግን “የእኔ ብሔረሰብ ከአንተ ይሻላል” እያልን የምንሰዳደብ ከሆነ የዓለም መጨረሻ ሆነን እንዳንቀር እሰጋለሁ።


እስኪ እኛም ትላልቅ ነገሮችን እንመኝ። አንዲት ኢትዮጵያን እንገንባ። ክልላችን ብሔርንና ቋንቋን ማዕከል ከማድረግ ይሻገር። በአንድ አገር ውስጥ እኩል ሥልጣን ያላቸውን መቶ ባንዲራዎች ከማውለብለብ ይልቅ አንድ ባንዲራ ይኑረን። ሌሎች የክልል ባንዲራዎች ቢኖሩን እንኳ እኩል ስፍራ አይሰጣቸው። ትንንሾቹ ባንዲራዎች ለትልቁና ለአንዱ ለኢትዮጵያ ባንዲራ ይገዙ። በእውቀት፥ በምርምር፥ በመሪነት፥ በንግድ፥ በስፖርት፥ በሕክምና፥ በፖለቲካ፥ በእርሻ፥ በሕግ፥ ወ.ዘ.ተ. የላቁ ኢትዮጵያውያንን እናፍራ።


የፖለቲካ ፓርቲዎችም ብሔርን ወይም የአንድን አካባቢ መሰረት ያደረገውን የፖለቲካ ተልእኮአቸውን መቀየር ያለባቸው ጊዜ አሁን እንደሆነ አምናለሁ። ብሔርንና ቋንቋን መሰረት ያደረገ ፖለቲካ አክሳሪነቱ ምን ያህል እንደሆነ ባለፉት ዓመታት አይተናል። ከመቼውም ጊዜ ይልቅ አገራችን ዛሬ በመንታ መንገድ ላይ እንዳለች አያለሁ። በዚህ ጊዜ በማስተዋል ከሄድንና ትክክለኛውን አቅጣጫ ከመረጥን ትልቅ የማደግ ዕድል ከፊታችን አለ።


በተጨማሪም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ውድድራቸው ሕዝብንና አገርን ለማሳደግ፥ ከሌላው ይልቅ የተሻለ ሀሳብና ራእይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለማቅረብ እንጂ በዬትኛውም መንገድ ሌላውን ሰው ሰድቦ፥ ጨፍልቆ፥ ወይም ገድሎ ሥልጣን መያዝ መሆን የለበትም። የኢትዮጵያውያን መድረኮች በእውቀት፥ በፈጠራ ችሎታ፥ እና በጥበብ የምንወዳደርበትና አንዱ ከሌላው የሚማርበት እንጂ የምንሰዳደብበት መሆን የለበትም።


ሌላው መዘንጋት የሌለብን ነገር ቢኖር ባደጉት አገሮች ፖለቲካ የሚመሩ ሰዎች ቀን ተጨቃጭቀው ውለው ማታ አብረው መብላት የሚያስችል የእውቀትና የፖለቲካ ብስለት አላቸው። እኛ ወደዚያ ደረጃ ገና ስላልደረስን የፖለቲካ አቋማችን ሌላውን በማንቋሽሻሽ ላይ የተመሰረተ እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል።


በመጨረሻም አንድን አገር በማሳደግ ረገድ ትምህርት የሚኖረውን ሚና በሌላ ፅሁፍ ይዤላችሁ እስከምመጣ እግዚአብሔር በቸርነቱ ይጠብቃችሁ።


»እስኪ በዚህ ጽሑፍ ዙሪያ እንወያይ።

ምን አዲስ ትምህርት አገኘህ(ሽ)? ምን ጥያቄ አለህ(ሽ)? መልሱን እኔ ብቻ አልመልስም። ሁላችንም አስተማሪዎች፥ ገንቢዎችና፥ መካሪዎች እንሁን። አንዱ የሌላውን ጥያቄ መመለስ ይችላል።

166 views0 comments