Search
  • Bekele Shanko

ኢትዮጵያ የአጭርና የረጅም ጊዜ ተግዳሮቶችዋን እንዴት ማስወገድ ትችላለች? ክፍል አንድ

Updated: Aug 18, 2018

አገራችን ኢትዮጵያ የሀብታም ድሃ፥ የታደለች መከረኛ፥ የውብ ጓስቋላ ናት። አስደናቂው ሕዝቧ፥ በተፈጥሮ ያገኘቻቸው ገጸ በረከቶች፥ በዘመናት ያካበተችው ታሪክ፥ በቅኝ ገዢዎች ያልተበረዘው ባሕል፥ በእግዚአብሔር ላይ ያለው የሕዝቧ እምነቷ፥ ወ.ዘ.ተ. ውበቶቿ ሲሆኑ፥ በአንጻሩ ደግሞ የኢኮኖሚ ድቀት፥ የትምህርትና የሥልጣኔ ኋላቀርነት፥ እና የረጅም ጊዜ ራእይ ቀርጸው የሚመሯት መሪዎች እጦት ከመከራዎቿ ጥቂቶቹ ናቸው።


ኢትዮጵያ ታላቅ ባለታሪክ፥ የአውሮፓውያንን የቅኝ ገዢዎች ሤራ ደጋግማ ያከሸፈች፥ በአፍሪካ ውስጥ ነጻነቷንና ክብሯን ጠብቃ የኖረች ብቸኛ አገር፤ ዓለምን ያስደነቁ የአክሱም ሐውልቶች፥ የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት፥ የጎንደር ቤተ መንግሥት እና የመሳሰሉ የታላላቅ ሥራዎች ባለቤት ናት።


የኢትዮጵያ ነገሥታትና ሕዝብ በየዘመናቱ ያጋጠሟቸውን ከፍተኛ ተግዳሮቶች በድል አልፈዋል። ለባልንጀራ ቸርነት አድርገዋል፥ ጠላትን አሸንፈዋል፥ ለአገርና ለሕዝብ ነጻነት ሲሉ ሕይወታቸውን ሰውተዋል፥ በጠላት እጅ ወድቀው ማላገጫ ከመሆን ክብራቸውን ጠብቀው በራሳቸው ሰይፍ ወድቀዋል፤ በመከራ ውስጥ የነበሩትን የቅርብና የሩቅ አገሮች አግዘዋል።


ለምሳሌ ያህል ኢትዮጵያዊ ንጉሥ አጼ ካሌብ በስድስተኛው ምዕተ ዓመት ከወታደሮቻቸው ጋር ቀይ ባሕር ተሻግረው በስደት ውስጥ የነበሩትን የየመን ክርስቲያኖች ከአይሁዶች እጅ ነጻ አውጥተዋል። በዘመነ መሳፍንት አገዛዝ ስትናወጥ የነበረችውን ኢትዮጵያን አንድና ታላቅ አገር አድርጎ የመምራት ራእይ የነበራቸው አጼ ቴዎድሮስ ለእንግሊዞች እጄን አልሰጥም በማለት በመቅደላ በራሳቸው ሰይፍ ወደቁ። ታላቁ የጦር መሪ ራስ አሉላ አባነጋ በዶጋሊ፥ በአድዋ፥ በጉንደት፥ በጉራ፥ በመተማ፥ በአምባ አላጌ፥ በመቀሌና በሌሎች ሥፍራዎች የግብጻውያንን፥ የሱዳኖችንና የጣሊያንን ሠራዊት ድል በማድረግ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር አስከብረዋል።


አጼ ዮሐንስ ለግብጾችና ለደርቡሾች አገር አልሸጥም በማለት ተዋግተው በክብር አልፈዋል። አጼ ሚኒልክ በግፍ ሊገዛን የመጣውን ጣሊያንን በአድዋ ላይ ድል በማድረግ ዓለምን ያስደነቀና የጥቁር ሕዝቦች ኩራት የሆነውን ታሪክ አስመዝግበዋል። እነዚህና የመሳሳሉ የኢትዮጵያ አባቶች በነፍሳቸው ተወራርደው ታላቅና የሚያኮራ ታሪክ አስረክበውናል። ኢትዮጵያ የጀግኖች ምድር ናት።


ነገር ግን በታሪክ እንደምንማረው ከውጭ የመጣ ጠላትን ማሸነፍ ለኢትዮጵያ ከባድ አልነበረም፥ ብዙ ጊዜ ትልቁ ችግሯ ግን የነበረው የውስጥ አንድነት ማጣት ነው። አንድነታችን ደግሞ ብዙ ጊዜ የታየው የውጭ ጠላት የመጣ ጊዜ እንጂ ኢትዮጵያን ተባብረን በልማት ጎዳና ለመምራት አልነበረም። ግን ለምን?

የአፍሪካ አገሮች ከአውሮፓውያን የቅኝ ግዛት ነጻ እንዲወጡ ኢትዮጵያ የበኩሏን አስተዋጽኦ አድርጋለች። ለሰው ልጆች ሰላምና እኩልነት ካላት ፍላጎት የተነሣ አገሮቻቸውን ከቅኝ ግዛት ነጻ ለማውጣት የታገሉትን ማንዴላንና ሙጋቤን የመሳሰሉትን የአፍሪካ የነጻነት ተዋጊዎች ረድታለች። ከኢትዮጵያ ብዙ ኪሎ ሜትር ርቃ የምትገኘዋን የደቡብ ኮሪያን አገር እንኳን ሳይቀር በችግሯ ጊዜ ደርሳለች። “ኢትዮጵያን በጣም እንወዳታለን፥ ኢትዮጵያ ባለውለታችን ናት” የሚሉ ብዙ የደቡብ ኮሪያ ዜጎች አጋጥመውኛል።


ነገር ግን ኢትዮጵያ ያለፈውን ታሪክ ብቻ እያወራች አትኖርም። ዛሬም ታሪክ መሥራት ትችላለች። ዛሬም ዓለምን ለማስደነቅ ዕድሉ አላት። ባለፉት ዘመናት በግፍ ሊገዙን በሞከሩ ሁሉ ላይ በመዝመት ነጻነቷን እንደጠበቀች፥ ዛሬም በጋራ ጠላቶቻችን ማለትም በድህነት፥ በኋላቀርነት፥ በዘረኝነት፥ በመሐይምነትና በጠባብ አመለካከቶች ላይ ታላቅ ዘመቻ በማድረግ ራሷን ነጻ ማድረግ ትችላለች።


ባለፉት አራት ወር የኢትዮጵያ ሕዝብ በተመስጦ የሰማቸው የሰላም፥ የፍቅርና የአንድነት ስብከቶች ፍሬ እንዲያፈሩ፥ የጥልን ግድግዳ አፍርሶ በአንድነቷ የጠነከረች ኢትዮጵያን በጋራ ለመገንባት የተጀመረው ጉዞ እንዲቀጥል፥ የኢትዮጵያዊነት መታወቂያችን የምናፍርበት ሳይሆን የምንኮራበት እንዲሆን፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ እንዳሉትም ጎበዝ ተማሪዎቻችን ቤተ መንግሥት የሚጎበኙበትና በትላልቅ ዓለም አቀፍ ዩኒቨርስቲዎች የነጻ ትምህርት ዕድል አግኝተው የአገራችንን እድገት የሚያፋጥኑበት ራእይ ግቡን እንዲመታ ምን መደረግ አለበት? በዛሬ ላይ ቆመን ነገን ስናይ፥ ኢትዮጵያ የአጭርና የረጅም ጊዜ ተግዳሮቶችዋን ለማስወገድ ምን ማድረግ ይጠበቅባታል? እነሆ ጥቂት አሳቦች፦


1. ከሁሉ አስቀድሞ በአገሪቷ ሰላምን ማስፈን


ሰላም ከሌለ ምንም ዓይነት በጎ ነገር ሊኖር አይችልም። ዛሬ በሕዝባችን መካከል የሚታየው አለመተማመን፥ መከፋፈል፥ ጥል፥ ሽብርና ጦርነት የሚጎዳው ሁላችንንም ነው። ቁስሉም ቶሎ አይሽርም። ሰላም የሌለው አገር ለትምህርት፥ ለዕድገትና ለብልጽግና ዕድል የለውም። ስለዚህም ሰላምን በምድራችን በአስቸኳይ ለማስፈን እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ድርሻውን መወጣት አለበት።


ለምሳሌ ያህል የሃይማኖት ተቋማት በሙሉ ሕዝባቸውን ማረጋጋትና ስለ ሰላም አጥብቀው ማስተማር ይኖርባቸዋል። “እያንዳንዱ ቤቱን ቢያጸዳ ከተማችን የጸዳች ትሆናለች” እንደተባለው መሆን አለበት። በተጨማሪም የሃይማኖት ተቋማት ጥቃት ለደረሰባቸውና ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን ከማንም ቀድመው የመድረስ ሃይማኖታዊ ጥሪና ኃላፊነት አለባቸው። እርዳታ ከኢትዮጵያ መንግሥት ወይም ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከመድረሱ በፊት ከቤተ ክርስቲያናትና ከመስጊዶች መድረስ አለበት ብዬ አምናለሁ።


እንዲሁም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በየቢሮአቸው በአስቸኳይ ሠራተኞቻቸውን ስለ ሰላም ማስተማርና ሽብር ፈጣሪዎች ወይም በሽብር ተሳታፊዎች እንዳይሆኑ ቃል ኪዳን ማስገባት ያስፈልጋል። ያኔ የሶቭየት ኅብረት አብዮት አገራችንን ባጥለቀለቀ ጊዜ እኮ የመንግሥት ሠራተኛው፥ ወጣቱ፥ ሴቱ፥ አስተማሪው፥ ተማሪው ሳይቀር የሶሻሊዝምን መጻሕፍት በግዴታ ያጠና ነበር። ዛሬስ ለኢትዮጵያ ሰላም፥ አንድነትና እድገት ሁላችን መማር፥ ማስተማር፥ መወያየት እና ለተግባራዊነቱም ራሳችንን መስጠት አንችልም ወይ? በእርግጥ እንችላለን።


በሕዝባችን መካከል በየቦታው የሚለኮሱ የጥላቻና የጠብ አጫሪነት እሳቶች በአስቸኳይ መጥፋት አለባቸው። በምድራችን የሰው ደም በከንቱ አይፍሰስ። በእግዚአብሔር አምሳል ለክብር የተፈጠርን ውብና ድንቅ መሆናችንን ዘንግተን ሰውን እንደ ቆሻሻ ነገር መቁጠር በአስቸኳይ መቆም አለበት። ጭካኔና አረመኔነት ከምድራችን ይወገዱ፥ አንዳችን ለሌላችን እንኑር። ያ ካልሆነ እግዚአብሔር ያዝንብናል፥ ያደጉት አገሮች ይታዘቡናል፥ የታሪክ ገጾቻችን መራራ ይሆናሉ።


እኛ ኢትዮጵያውያን ሁላችንም ድሃ ነን፥ ሁላችንም ተበድለናል፥ ሁላችንም ተንቀናል። በምድራችን ኦሮሞው፥ አማራው፥ ሶማሌው፥ ትግሬው፥ ሲዳማው፥ ጉራጌው፥ ወላይታው፥ ሃዲያው፥ ከምባታው፥ አፋሩ፥ ጌዴኦው፥ ጋሞው እና የተቀረውም እያንዳንዱ ብሔረሰብ የመጨረሻ ድሃና ጓስቋላ ነው። የአማራ ልጆች በአንድ ወቅት ፖለቲካውን ስለመሩ የአማራው ሕዝብ ሀብታም አልሆነም፥ ወይም በሌላ ጊዜ የትግሬ ልጆች አገር ስለመሩ የትግሬው ሕዝብ አላለፈለትም።


ምናልባት የሕዝብን ሀብት ያላግባብ የሰበሰቡ ጥቂቶች አልፎላቸው ሊሆን ይችላል። ያም ቢሆን ጊዜያዊ እንጂ ዘለቄታዊ ሀብት አይደለም። በግፍ ንብረት የሚሰበስቡ ሳይበሉ እንደሚሞቱ የታሪክ ገጾች ይመስከራሉ። የውጭ ጠላት በመጣብን ጊዜ ሁሉ እንደ አንድ ሰው ወጥተን ጠላትን አሸንፈን የአገርን ነጻነት እንዳስጠበቅን አሁን ደግሞ በሰላምና በፍቅር ተሳስረን በጋራ ጠላቶቻችን ላይ ማለትም በድህነት፥ በዘረኝነትና በኋላ ቀርነት ላይ ዘምተን ከእነዚህ ጠንቆች ራሳችንን፥ አገራችንንና ወደፊት ሊፈጠር ያለውን ታሪካችንን ነጻ እናውጣ።


በዚህ ሰላምን በማስፈኑ ዘመቻ እስከዛሬም እንዳደረጉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትልቅ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ። ምናልባት እንዳይናገሩና እንዳይሠሩ ያገዳቸው አካል ከሌለ ማለቴ ነው። እንደዚህም ዓይነቱ ነገር ሊኖር እንደሚችል አገሮቻቸውን ለማሳደግ ትልቅ ራእይ አንግበው ተነሥተው በነበሩ በኮንጎው መሪ ፓትሪክ ሉሙምባ እና በጋናዊው ኩዋሜ እንክሩማ የደረሰባቸውን ታሪክ ይመሰክራል። ዶ/ር ዐቢይ (መሥራት በሚያስችላቸው ሁኔታ ላይ ካሉ) እና እርሳቸውና አብረዋቸው የሚሠሩ አካላት ቅድሚያ እየሰጡ ከሕግ ባለሙያዎች፥ ከአስተማሪዎች፥ ከወጣት መሪዎች፥ ከንግዱ ማሕረሰብ አባላት፥ ከሃይማኖት አባቶች፥ ከጸጥታ ኃይሎች፥ እና ከሚመለከታቸው ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በየፊናው ውይይት ማድረግ፥ አስፈላጊ የሆኑ ውሳኔዎች ላይ መድረስና ኃላፊነቶችን መከፋፈል ያስፈልጋል።


2. ረጅም ሕንጻ ከመገንባት በፊት አስተማማኝ መሠረት መጣል ያስፈልጋል


ባለፉት አራት ወራት የሰማናቸው ተስፋዎች ልባችንን አሙቀዋል፥ ድህነታችንንም ለጊዜው እንድንረሳ አድርገውናል። እነዚህ ተስፋዎች ከ100 ፎቆች በላይ ርዝመት ያለውን ሕንጻ ለመገንባት እንደተነሣ ሰው ያክል አርቀን እንድንመኝ አድርገውናል። ለምሳሌ ያህል ተቃዋሚ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተፎካካሪ ለመሆን ከስደት ምድር ወደ አገር ቤት በመግባት ላይ ናቸው። ይህም ትልቅ ድል ስለሆነ በጣም ደስ ብሎኛል። ነገር ግን መንግሥት ከእነዚህ ተፎካካሪ ኃይሎች ጋር ሰፊ ውይይት ማድረግና የጋራ የሆኑ አገራዊ መመሪያዎችን ማዘጋጀት ይጠበቅበታል። ይህም መሆን ያለበት ነገ ሳይሆን ዛሬ ነው።


በተጨማሪም የአገሪቱን ለውጥ የሚመራው ቡድን ባለፉት 27 ዓመታት ከመሩ ሰዎች ጋር አስፈላጊ ውይይቶችንና ስምምነቶችን ማድረግ የኢትዮጵያን አንድነት ያጠነክራል፥ የለውጡን ሂደት ያፋጥናል፤ በሰው፥ በንብረትና በታሪክ ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ጥፋቶችን ይቀንሳል። እንዲሁም መስከረም ወር ትምህርት ቤቶች ከመከፈታቸው በፊት በመላ አገሪቱ ውስጥ ለሚገኙ አስተማሪዎች በተቻለ መንገድና ፍጥነት የራእይና የስልጠና ኮንፍራንሶች ቢዘጋጁና አስተማሪዎችን የለውጡ አራማጆች አድርጎ ማሰለፍ ቢቻል እጅግ ይጠቅማል ብዬ አምናለሁ።


3. ከማውራት ይልቅ መሥራት


ለመሥራት የምናስባቸውን ነገሮች አስቀድሞ መናገር አንዳንዴ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል። ኢትዮጵያ አድጋ፥ የራሷን ሀብት በራሷ ማስተዳደር የማያስደስታቸው ቡድኖች በቅርብም በሩቅም ሊኖሩ ይችላሉና አፋችንን ዘግተን ሥራችንን መሥራት ያስፈልጋል። ለምሳሌ ያህል በአፍሪካ ውስጥ ቦትስዋና የምትባል አገር መኖርዋን ብዙዎች አያውቁም። ለምን? የቦትስዋና መሪዎች የአገራቸውን ራእይ ለዓለም አያሰራጩም። አፋቸውን ዘግተው በሥራቸው ላይ ትኩረት ከማድረጋቸው የተነሣ ብዙ ጠላት የለባቸውም። የአገራቸውም ኢኮኖሚ እጅግ ጠንካራ ነው። ዛሬ ቦትስዋና ምንም ዓይነት ምርት ማምረት ብታቆም የአገሪቷን ሕዝብ በሙሉ ለሃያ ስምንት ዓመት መመገብ የሚችል ሀብት በባንካቸው እንደሚገኝ ይገመታል።


በተጨማሪም ባለፉት 27 ዓመታት ስር የሰደዱ የዘረኝነት ችግሮቻችን በአንድ ሌሊት ሊጠፉ እንደማይችሉ አውቀን በጥበብ፥ በትዕግስትና በማስተዋል ሕዝባችንንና አገራችንን ለማሳደግ እያንዳንዳችን የበኩላችንን መሥራት ይኖርብናል። መከፋፈልን፥ መበታተንን፥ ዘረኝነትን፥ ቂምንና ጥላቻን እምቢ በማለት፥ እግዚአብሔር ምሕረቱን በሕይወታችንና በምድራችን እንዲያፈስ እየጸለይን፥ ለተቸገሩት በፍጥነት እየደረስን መልካም ምሳሌዎች ለመሆን እንነሣ። እግዚአብሔር እንቆቅልሻችንን ይፍታ፥ ሕዝባችንን ከክፉ ይጠብቅ፥ ሰላሙንም ይስጠን፥ ለዓለምም በረከት ያድርገን። በሚቀጥለው እስከምንገናኝ ደኅና ሰንብቱልኝ።

209 views0 comments