Search
  • Bekele Shanko

ኢትዮጵያና ኮሮና ቫይረስ

Updated: Mar 21, 2020

ጤና ይስጥልኝ።

ኮሮናቫይረስን ስለ መከላከል የኢትዮጵያ መንግሥት፥ የጤና ባለሙያዎችና ድርጅቶች እንዲሁም የተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አስፈላጊ የሆነውን ሁሉ እያደረጉ እንዳሉ አምናለሁ። ነገር ግን እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ያሉ አገሮች መላውን ዓለም በአጭር ጊዜ ያጥለቀለቀውን ወረርሽኝ የመከላከል የገንዘብና የሕክምና መሰረተ ልማት እቅማችን ውስን በመሆኑ በሽታው በፍጥነት በሀገራችን እንዳይዛመት ካለኝ ስጋት በግልና በሕብረት ማድረግ በሚገባን ላይ ትኩረት እንድናደርግ የበኩሌን ምክር በዚህች አጭር ጽሁፍ ለማካፈል ወደድኩኝ።

ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ ዓለም በከፍተኛ ፍጥነት ተቀይሯል። ሰዎች ከቦታ ወደ ቦታ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ተገድቧል። ብዙ ሀገሮች በራቸውን ዘግተዋል። የአየር፥ የባህርና የየብስ የሕዝብ ማመላለሻዎች ሥራቸውን ቀንሰዋል ወይንም እቁመዋል። በብዙ ሥፍራዎች ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል። ምግብ ቤቶች፥ ሆቴሎች፥ ቡና ቤቶች የመሳሰሉ የአገልግሎት ተቋማት ሥራቸውን አቁመዋል አሊያም የአገልግሎት አሰጣጥ ሁኔታቸውን ቀይረዋል። የዓለም ገበያ ላሽቋል።

በሽታውን ለማቆም ምን ያህል ጊዜ እንደሚፈጅ፥ ነገ ምን ሊሆን እንደሚችል፥ ወይም በሕይወትና በገንዘብ ምን ያህል ሊያስከፍል እንደሚችል ማንም አያውቅም። የሰው እውቀት፥ ሥልጣንና ገንዘብ ሊያድነን እንደማይችል በግልጽ ታይቷል። በሽታው የቆዳ ቀለምን፥ ቋንቃን፥ የሀብት አቅምን፥ ሃይማኖትን፥ ሀገርን፥ ብሔርንና የፖለቲካ ዝንባሌን ሳይለይ የሰውን ልጆች ሁሉ እየተገዳደረ ያለ የጋራ ጠላት ነው።

ታዲያ በዚህ ጊዜ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ምን ማድረግ አለባቸው? ከእያንዳንዳችንስ ምን ይጠበቃል? ራሳችንንና ሕዝባችንን እንዴት ከዚህ መቅሰፍት መጠበቅ እንችላለን? እነሆ አራት ነገሮች፦

ፍርሃትን ማስወገድ

ዛሬ ከዚህ በሽታ የተነሣ ብዙ ሰዎች በትልቅ ፍርሃት ውስጥ ይገኛሉ። የምንሰማው ሁሉ የሚያሰፈራ ነው። ከበሽታው ይልቅ ትልቁ ጠላታችን ፍርሃት ሆኗል። ነገር ግን ፍርሃት ወደ ትክክለኛ ጥንቃቄ እንዲመራን እንጂ ነፍሳችንን እንዲያስጨንቅ መፍቀድ የለብንም። ፍርሃት በትክክል ካልተያዘ ሰውን ሊጎዳ እንደሚችል መዘንጋት የለብንም። ለዚህም ሊሆን ይችላል “አትፍራ” የሚለው ትእዛዝ ወይም ምክር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 365 ጊዜ የተጻፈው (ለእያንዳንዱ ቀን አንድ ማለት ነው)።

ስለዚህ ተገቢውን ጥንቃቄ ልናደርግ እንጂ በፍርሃት ልንዋጥ አያስፈልግም። አእምሮአችን በፍርሃት እንዳይዋጥ ደስታን የሚሰጡ ነገሮችን ማድረግ፥ ለምሳሌ ከምንወዳቸው ሰዎች ጋር ማውራትና መጸለይ (በስልክ ወይም በኢንተርኔት ሊሆን ይችላል)፥ መጻሕፍትን ማንበብና በአእምሮአችን መልካም ነገሮችን ማስተናገድ ያስፈልጋል።

ሁሉን ወደሚችል አምላክ መጸለይ

እኛ የሰው ልጆች በእውቀታችንና በጥበባችን ውስን ነን። እግዚአብሔር ግን ሁሉን ያውቃል፥ ሁሉንም ይችላል። ይህ ክፉ በሽታ እንዴትና ለምን እንደተከሰተ እግዚአብሔር ያውቃል። እግዚአብሔር የማያውቀው፥ የማይገዛው፥ የማይቆጣጠረው ምንም ነገር የለም። እርሱ ሁሉን ቻይ ነው። መቅሰፍትን ሊያስወግድ፥ የታመመን ሊፈውስ፥ ያዘነን ሊያጽናና የሚችል አምላክ ነው። ስለዚህ እጃችንን ከልባችን ጋር ወደ እርሱ እናንሣ፥ ከእርሱም ምህረትን እንለምን፥ በተስፋ ቃሉም እንመን።

የተስፋ ቃሉም እንዲህ ይላል፦ “ዝናብ እንዳይወርድ ሰማያቱን ብዘጋ፥ ወይም ምድሪቱን ይበላ ዘንድ አንበጣን ባዝዘው፥ ወይም በሕዝብ ላይ ቸነፈር ብሰድድ፥ በስሜ የተጠሩት ሕዝቤ ሰውነታቸውን አዋርደው ቢጸልዩ፥ ፊቴንም ቢፈልጉ፥ ከክፉ መንገዳቸውም ቢመለሱ፥ በሰማይ ሆኜ እሰማለሁ፥ ኃጢአታቸውንም ይቅር እላለሁ፥ ምድራቸውንም እፈውሳለሁ።” (2 ዜና 7፡13-14)

ስለዚህ እግዚአብሔር በቃሉ መሰረት ጸሎታችንን ሰምቶ እንደሚመልስ በማመን፥ ከእኛም የሚጠበቀውን (ማለትም ራስን ማዋረድ፥ እግዚአብሔርን መፈለግ፥ ከክፉ መንገድ መመለስ) ሆነን በመገኝት ለራሳችን፥ ለቤተሰባችን፥ ለሕዝባችንና፥ ለመላው ዓለም እንጸልይ።

ለራስ፥ ለቤተስና በቅርባችን ላሉ ሰዎች ጤንነት ጥንቃቄ ማድረግ

ምን ዓይነት ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባን የመንግሥት ቢሮዎች፥ የጤና ተቋማትና፥ የጥናትና ምርምር ድርጅቶች፥ እናም ሌሎች በየጊዜው የሚሰጡንን መመሪያ በሚገባ ማወቅና መከታተል ያስፈልጋል። እስካሁን የታወቁ ዋና ዋናዎቹ የመከለካያ መንገዶች ብዙ ሰዎች ባሉበት አለመገኘት ወይም በሁለት ሰዎች መካከል የሁለት ሜትር ያህል ርቀት መጠበቅ፥ የበሽታው ምልክቶች ያለበት ሰው ከሆነ ለሁለት ሳምንት ራስን ከሰው ማግለል፥ ወደ አየር አለማስነጠስ፥ እጅን በውሃና በሳሙና ቶሎ ቶሎ መታጠብ፥ እንዲሁም ትኩሳት፥ ሳል፥ የመተንፈስ ችግርና የአቅም ድካም የመሳሳሉ ምልክቶች የታየበት ሰው ቶሎ ህክምና ማግኘት ናቸው።

በተጨማሪም በእንደዚህ ዓይነቱ የችግር ጊዜ ለራሳችን ብቻ መጠንቀቅ ሳይሆን ለሌሎች ጥንቃቄን ማድረግና የምንችለውን ሁሉ በጎነት ማሳየት ያስፈልጋል። ለምሳሌ የምግብ ዕቃዎች እንኳን ስንገዛ ለራስ ብቻ ማሰብና ማከማቸት ሳይሆን ለሌሎች ማሰብ እና ያለንን እንኳ ማካፈል ተገቢ ነው።

እኛ ደግሞ በባሕላችንም ከሰዎች ርቀን መኖር ሰለማንችል፤ በቡናውም፥ በለቅሶውም፥ በታክሲውም፥ በአውቶቡሱም ከብዙ ሰው ጋር ስለምንገናኝ በጣም ያሳስበኛል። ስለዚህ ይህ ክፉ አየር እስከሚወገድልን ድረስ ትልቅ ጥንቃቄ ብናደርግ ራሳችንን ብቻ ሳይሆን ትውልዱን ከጥፋት መታደግ እንችላለን።

በአንድነት መቆም

የኮረናቫይረስ ወረርሽኝ ማንንም የማይለይ፤ በፆታ፥ በሀገር፥ በቋንቋ፥ በፖለቲካ፥ በዘር፥ በሃይማኖት ያልተገደበ የጋራ ጠላት ነው። ስለዚህም እኛም ከሰሜን እስከ ደቡብ፥ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ፥ እንደ እንደ አንድ ሕዝብ ሆነን፥ የጋራ ጠላት በጋራ መከላከልና መዋጋት ያስፈልጋል። ይህን ማድረግ ካልቻልን ግን ችግሩ እጅግ አስከፊ ሊሆን እንደሚችል መገመት ያስፈልጋል።

ለምሳሌ ያህል ይህን በምጽፍበት ጊዜ የአሜሪካን መንግሥት ከፍተኛ ገንዘብ ለበሽታው መከለከያ በመመደብ ላይ ይገኛል። ተቃራኒ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአንድነት ለመሥራት ችለዋል። ምሁራን፥ የንግዱ ማህረሰብ፥ እና የግልና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከመንግሥት ጋር በጋራ በመሥራት ላይ ይገኛሉ። ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ በአንድነት ሕዝብን ከበሽታው ለመጠበቅ በመሥራት ላይ ይገኛሉ።

እኛ ኢትዮጵያውያን እንደዚህ ዓይነቱ የገንዘብ አቅም የለንም። ነገር ግን መልካም እረኛ የሆነው እግዚአብሔር አለ፤ ማንኛውንም የጋራ ጠላት በጋራ መመከት ልማዱ የሆነ ሕዝብ አለን፤ ከራሱ ይልቅ ለሌላው የሚያስብና መከራን ማሸነፍ የሚችል ሕዝብ አለን።

ስለዚህ ክፉ ፍርሃትን በማስወገድ፥ ሁሉን ወደሚችል አምላክ በመጸለይ፥ መንግሥትና የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡንን ምክርና መመሪያ ተግባራዊ በማድረግ፥ እና ሁላችን እንደ አንድ ሕዝብ በጋራ በመቆምና እንዳችን ለሌላችን ደህንንት የምንችለውን ሁሉ በማድረግ ይህን የጋራ ጠላት የሆነውን ኮሮናቫይረስ በጋራ እንዋጋ። ሁሉን የሚችል አምላክ በዙፋኑ አለና በእርሱ እንመካ።

እግዚአብሔር አምላካችን እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ እንዲሁም በአምሳሉ የተፈጠረውን የሰውን ዘር ሁሉ ከመቅሰፍት እንዲጠብቅ፥ መቅሰፍቱንም ከላያችን እንዲያስወግድልን፥ ለመሪዎቻችንም መለኮታዊ ጥበብ እንዲሰጣቸው ጸሎቴ ነው።

በተጨማሪም መጋቢ ተስፋዬ ጋቢሶ በአብዮቱ ዘመን የዘመረውን ይህን መዝሙር ማንጎራጎር ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ።

“ሕዝቤ ሆይ ና ይላል እግዚአብሔር
ወደ ቤትህ ግባ ከግርግር
ጥላ ልሁንልህ ከጠራራው ፀሀይ
ከጥፋት ውሽንፍር"

ዶ/ር በቀለ ሻንቆ

ግሎባል አካዳሚ ፎር ትራንስፎርሜሽናል ሊደርሺፕ (GATL)

ትሬዚዳንት

Photo by

Avel Chuklanov

on

Unsplash

73 views0 comments