Search
  • Bekele Shanko

የኢትዮጵያና የኤርትራ ሰላም ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች አራቱ

Updated: Jul 24, 2018

1. ጥላቻ በፍቅር ይተካል

ከሁለት ቀናት በፊት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ኤርትራ ሲገቡ ከአይሮፕላን ማረፊያ አንስቶ በአስመራ መንገዶች እስከ ቤተ መንግሥት ድረስ በኤርትራውያን ወገኖቻችን ፊት የታየውን ታላቅ ደስታና ተስፋ ማየት ምንኛ ያስደስታል! ህጻናት፥ ወጣቶች፥ እናቶች፥ አባቶች፥ ምሁራን

፥ የፖለቲካ መሪዎች፥ ወዘተ ዘንባባና የሁለቱን አገሮች ባንዲራዎች እያውለበለቡ፥ የሰላምን መዝሙር እየዘመሩና የደስታ እንባ እየተናነቃቸው የአስመራን መንገዶች ሲያጣብቡ፥ በአንጻሩም ደግሞ ኢትዮጵያውን በያሉበት ሁሉ ይህን ታላቅ ቀን ሲመሰክሩ ከማየት የተሻለ ምን ነገር አለ? የአረንጓዴ፥ ቢጫ፥ ቀይ ባንዲራችንን በጭራው አንግቦና ድምጽ አልባው የኢትዮጵያ አምባሳዳር ሆኖ በዓለም ታላላቅ ከተሞች የሚታየው አይሮፕላናችን በአስመራ አይሮፕላን ጣቢያ አርፎ ስታዩስ ምን ተሰማችሁ? እጅግ አያምርም ነበር? ጦርነት በሰላም፥ ጥላቻ በፍቅር፥ ቂም በይቅርታ፥ ኀዘን በደስታ ተለወጠ ማለት ይሄ ነው! እኔ ፕሬዚዳንት ኢሳያስን ለመጀመሪያ ጊዜ በቴሌቪዥን ካየኋቸው ጊዜ አንስቶ እንደዚህ ቀን በደስታ ሲፈነጥዙ አይቼ አላውቅም ብል ማጋነን አይሆንም። ምናልባት በዚህ ቀን ከታየው ፍቅርና ደስታ የተነሣ በፕሬዚዳንት ኢሳያስ ዕድሜ ላይ ዓመታት ይጨመራሉ ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ፍቅር፥ ሰላም፥ ደስታና ሳቅ ዕድሜ ቀጣዮች ናቸውና።በዓይናችን ይህንን ያሳየን፥ ዶ/ር አብይን ለዚህ ትልቅ ዓላማ የጠራው የሰማይና የምድር ፈጣሪ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን! እኛ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን፥ እንዲሁም የሰውን ልጆች ሁሉ ሰላምና እድገት የምትመኙ ሁላችሁ፥ እንኳን ደስ አለን። ሳንሞት ይህን ጊዜ ያሳየን እግዚአብሔር እንዴት ቸር ነው!

2. የመንከራታት ዘመን ያበቃል

ሰላም ማጣትና ጦርነት ቤተሰብን፥ ሕዝብንና አገርን ለብዙ ቀውስ ይዳርጋል። በሁለቱ አገሮች መካከል በተፈጠረው ግጭትና ጦርነት ምክንያት ብዙ ሰዎች ለተለያዩ ችግሮች ተዳርዋል። ከእነዚህም ችግሮች መካከል የኤርትራ ወጣቶች ለውትድርና እሳት ማገዶ እንዳይሆኑ በመስጋትና የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ከአገር በመሰደድ በሊቢያ፥ በግብጽ፥ በሱዳን በረሃዎች የወደቁ፥ ከበረሃ የተረፉት በባሕር የሰመጡ፥ ከባሕር ያመለጡት ደግሞ በተለያዩ አገሮች በእስር የማቀቁ ስንቶች ናቸው?“የስደተኞች መርከብ በባሕር ተገልብጦ ብዙዎች ሞቱ” የሚል ዜና በተሰማ ጊዜ ሁሉ የኤርትራውያንና የኢትዮጵያውን ስም በመስማታችን ልባችን የተሰበረበት፥ አንገታችንን ያቀረቀርንበት፥ “እግዚአብሔር ሆይ እባክህ አዲስ ቀን አምጣልን” እያልን ያለቀስንበት ቀን ስንት ነው? አሁን ግን ባለፉት ሦስት ወራት ያየናቸው መልካም ነገሮች የመንከረታት፥ የመቅበዝበዝና የመናቅ ዘመናችን ማክተሚያ የምሥራች እንደሆኑ ይሰማኛል።ከዚህ በኋላ የኤርትራ ወጣቶች፥ የወደፊት የአገሪቱ ተረካቢዎችና መሪዎች፥ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ለመዋጋት ወይም ከኢትዮጵያውያን ራሳቸውን ለመጠበቅ እያሉ ለውትድርና አይመለመሉም ብዬ አምናለሁ። ከዚህ በኋላ ጊዜያቸውን ለትምህርት፥ አእምሮአቸውን ለምርምር፥ እጃቸውን ለልማት እንጂ በባድሜ ሜዳና ዋሻ አይንከራተቱም። ከዚህ በኋላ ከኤርትራ ወጣቶች የተነሣ ኤርትራ ትለመልማለች ብዬ አምናለሁ።በነገራችን ላይ የብዙ ሺህ ወታደሮች ደም የፈሰሰባት ያች መከረኛዋ ባድሜ እንዲሁ በታሪክ ተመዝግባ ብቻ የምትቀር ባትሆንና ለምሳሌ ያህል የሁለቱን አገሮች እና የአፍሪካን ሕዝቦች የሚገለግል፥ በጥራቱ በዓለም ተወዳዳሪ የሆነ፥ የአፍሪካ የወደፊት የፖለቲካ መሪዎች የሚሰለጥኑበት (Africa Public Leadership University - APLU) በዚያ ሥፍራ ቢቋቋምና የወታደሮቻችን ደም አዲስቷን አፍሪካ ለመፍጠር የተከፈለ ዋጋ እንዲሆን ብናደርግስ? አዲስ አበባንና አስመራን የሚያገናኝ የባቡር መንገድስ በባድሜ እንዲያልፍ ቢታሰብ? ዶ/ር አቢይ፦ ትንሽ የእረፍት ጊዜ ሲያገኙ ያስቡበት እላለሁ። እስካሁን ካላሰቡበት ማለቴ ነው።

3. ወታደሮቻችን ራሳቸውንና አገርን ያለማሉ

በኤርትራና በኢትዮጵያ ዕርቅና ሰላም ምክንያት የሚገኘው ሌላው ትልቅ ጥቅም በድንበር ያሉ ወታደሮቻችን ወደ ቤተሰቦቻቸው ይመለሳሉ፥ ትምህርት ይማራሉ፥ ንግድ ይጀምራሉ፥ ራሳቸውንና አገራቸውን ያሳድጋሉ፥ አገር ይመራሉ፥ ግብርናችን በእውቀትና በቴክኖሎጂ የተደገፈና የተሻለ ምርት የሚገኝበት እንዲሆን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።ያለን ጥቂቱ ገንዘባችን ከዚህ በኋላ የሚወጣው ወታደሮችን በሕይወት ለማኖርና በጦር መሣሪያ ለማስታጠቅ ሳይሆን በሁለቱ አገሮች የትምህርትን ጥራት ለማሳደግ፥ መጻሕፍትንና ኮምፒዩተሮችን ለትምህርት ቤቶቻችን ለመግዛት፥ ለአስተማሪዎች ተጨማሪ የሙያ ብቃት ስልጠና ለመስጠት፥ ምርምርንና ዕውቀትን ለማሳደግ፥ ዶ/ር ዐቢይ እንዳሉትም ከፍተኛ ውጤት የሚያስመዘግቡ ተማሪዎች ቤተ መንግሥት እንዲጎበኙና እስኮላርሺፕ እንዲያገኙ፥ እንዲሁም ከላይ የጠቀስኩትን የባድሜን ዩኒቨርስቲ ለመገንባት ይውላል ብዬ አምናለሁ።

4. የሁለቱን፥ የአካባቢውንና የዓለም አገሮችን ልማት ያፋጥናል

የኤርትራና የኢትዮጵያ እርቅና ሰላም ጥቅሙ ለሁለቱ አገሮች ብቻ አይደለም። በሁለቱ አገሮች መካከል የሚኖረው ፍቅር ለሶማሊያ፥ ለጅቡቲ፥ ለደቡብ ሱዳን፥ ለሱዳን፥ ለኬንያ፥ ለሰሜን አፍሪቃና ለመካከለኛ ምስራቅ አገሮች እንዲሁም ለዓለም ሁሉ ጠቃሚ ነው። ሰላም ሲኖር ሰው በሕይወት መኖር፥ መማር፥ መሥራት፥ ማደግ እና አገሩን ማሳደግ ይችላል። በሰላም የሚኖር ሰው የተጣለን ለማስታረቅ ጊዜ፥ አቅምና መልካም ስም ይኖረዋል።ለምሳሌ ያህል ሁለቱ አገሮች በፍቅር ከኖሩ ኤርትራ የኢትዮጵያን ዓማጽያን ኃይሎች በሱዳን አታደራጅም፥ የሶማሊያን ሽብር ፈጣሪዎች በመደገፍ ገንዘቧን አታባክንም። ኢትዮጵያም ጸረ ኤርትራ የሆኑ ሥራዎችን በመሥራት ሀብቷን አታጠፋም። ከእንግዲህ የኢትዮጵያ ጤፍ ወደ ኤርትራ በየመንና በዱባይ በኩል ዞሮና ዋጋው ብዙ እጥፍ ሆኖ አይደርስም፤ በቀጥታ እንጂ። ሰላም ካለ በአገሮች መካከል የትምህርት፥ የልምድና የንግድ ልውውጦች ይደረጋሉ፤ የአሰብና የምጽዋ ወደቦች በመርከቦች ይሞላሉ፤ በኢትዮጵያውያን ገንዘብ ትላልቅ ሆቴሎች በአስመራ ይሠራሉ፤ በኤርትራውያን ገንዘብ ፋብሪካዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ይከፈታሉ፤ በኤርትራ የአየር ክልል የኢትዮጵያ አይሮፕላኖች ይርመሰመሳሉ፤ ቱሪስቶች በአንድ የጉዞ ዕቅድ ወይም ፓኬጅ ከነጭ ሳር እስከ ቀይ ባሕር አገር ይጎበኛሉ። ይህን ሁሉ የምናስብበት ጊዜ ደረሰ። አይደንቅም? ነገር ግን ይህ ሁሉ እንዲፈጸም እያንዳንዳችን የበኩላችንን ኃላፊነት በሚገባ መወጣት ይኖርብናል። ዶ/ር ዐብይን መውደዳችንን በሥራ እንግለጥ። በግላችን፥ በቤተሰብ፥ በቤተ ክርስቲያንና በእምነት ክፍሎቻችን ሁሉ ጸሎታችን ይቀጥል። መልካም የሆነውን የማይፈልግ አለና። ተማሪዎች ጠንክረን እንማር። አስተማሪዎች በብቃትና ከሙስና ነጻ በሆነ ሁኔታ እናስተምር። እኛም እንደ ጠቅላይ ሚኒስትራችን በያለንበት ፍቅርን፥ ሰላምንና ትህትናን እንስበክ። የምንሠራውን ሥራ ሁሉ በታማኝነትና በፍጹም ልብ እንሥራ። በአስተሳሰባችንና በአመለካከታችን ተለውጠን ለፍቅርና ለሰላም እንኑር። በመጨረሻም ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ መልእክት አለኝ። ይህ ቀን ለሁላችንም የደስታ ቀን ነው። በአገሮቻችን ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የሚጻፍበት ጊዜ ነው። በዚህ ጊዜ ኤርትራውያን ሁሉ የደስታው ተካፋዮች ሊሆኑ ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ። እባክዎን በእሥር ቤት ያሉትን ሰዎች በተለይም በእምነታቸው ምክንያት የታሠሩትን ቢፈቷቸውና ከቤተሰቦቻቸው ቢቀላቅሏቸው ደስታችን የላቀ ይሆናል። የእነርሱ ነጻነትና ደስታ የእርስዎም ነጻነትና ደስታ ነውና። በተቻለ መጠን እሥር ቤቶች ባዶ ቢሆኑስ? ምሕረት ቢደረግላቸውስ? እነርሱም አገርንና ትውልድን ከሕዝቡ ጋር አብረው ቢያለሙስ በፍቅር፥ በትልቅ ትህትናና በመልካም ራእይ የሚመሩንን ዶ/ር ዐቢይን እግዚአብሔር በሰላም ያኑርልን፤ ለኖቤል ሽልማት ብቻ ሳይሆን ለሰማያዊው የጽድቅ አክሊል ያብቃልን! ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በጣም ደስ ብሎናልና እናመሰግኖታለን። አዲስ ኤርትራ፥ አዲስ ኢትዮጵያ፥ አዲስ አፍሪካ! እግዚአብሔር ያድርግልን። ደህና ሰንብቱ።

11 views0 comments