Search
  • Bekele Shanko

ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያ ሙሴ ናቸውን?

Updated: Aug 6, 2018በዚህች አጭር ጽሁፍ ዶ/ር ዐቢይ የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ ባርነት ነጻ ካወጣቸው ሙሴ ጋር ተመሳሳይነት አላቸው ወይስ የላቸውም የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ እሞክራለሁ። ተመሳሳይነት ካላቸውስ ከሙሴ ሕይወትና አመራር ምን ሊማሩ ይችላሉ? እኛስ የዶ/ር ዐቢይ ደጋፊዎችና ተከታዮች እስራኤላውያን ከሙሴ ጋር ከነበራቸው ግንኙነትስ ምን እንማራለን?


ያሉኝን ነጥቦች ከማቅረቤ በፊት ግን የሙሴን የአርባ ዓመታት አመራር ከዶ/ር ዐቢይ አራት ወራት አመራር ጋር ማነጻጸር በራሱ ችግር እንዳለበት ለመግለጽ እወዳለሁ። ሙሴ ኃላፊነቱን የፈጸመ ሲሆን ዶ/ር ዐቢይ ገና እየጀመሩ ናቸውና። ባለፉት ሦስትና አራት ወራት በዶ/ር ዐቢይ አመራር የተገነዘብኳቸውን ነገሮች ከሙሴ አመራር ጋር ሳነጻጽር እግዚአብሔር ሕይወታቸውንና አመራራቸውን እንደ ሙሴ እንዲያደርግላቸው ጸሎቴን በማከል ነው።1.ሁለቱም በድንገት ለከፍተኛ አመራር ተጠሩ


ሙሴ የ40 ዓመት ጎልማሳ ሆኖ በግብጽ ቤተ መንግሥት ውስጥ በነበረበት ጊዜ የራሱ ወገን የሆነውን የእስራኤልን ሕዝብ ለመርዳት ፈለገ። ነገር ግን ወገኖቹ ስላልተቀበሉት ካደገበት አገር ተሰዶ 40 ዓመታት በበግ ጥበቃ አሳለፈ። በዚህም ምክንያት ወገኑን ለመታደግ የነበረውን ራእይ ረሳ። ሙሴ ራእዩን መርሳት ብቻ ሳይሆን የእስራኤልም ሕዝብ ሙሴን ሳይረሳው አይቀርም ብዬ አስባለሁ። ሙሴ ከዕለታት አንድ ቀን መሪ ሆኖ ይመጣልናል የሚል አሳብ ነበራቸው ብዬ አላስብም።


እግዚአብሔር ግን የሕዝቡን ሰቆቃ አይቶ ከሰማይ ወረደ። ሙሴንም በድንገት ለመሪነት ጠራው። ሕዝቡንም ከባርነት እንዲያወጣ ወደ ግብጽ ላከው። የሙሴ መመረጥ በእግዚአብሔር ዘንድ የታቀደ ቢሆንም በራሱ በሙሴም ሆነ በእስራኤላውያን ዘንድ ግን ያልተጠበቀ ነበር።


በተመሳሳይ ሁኔታም ምናልባት ከእናታቸውና በቅርብ ከሚያውቋቸው በቀር ዶ/ር ዐቢይ አንድ ቀን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ ብሎ ያሰበ ኢትዮጵያዊ ብዙ አልነበረም። በፈርዖን ቤተ መንግሥት የደገውን ሙሴን እስራኤልን እንዲታደግ ወደ ፈርዖን መልሶ እንደላከው ሁሉ ይቅርታን፥ ፍቅርን፥ ሰላምንና አንድነትን እንዲሰብኩ እግዚአብሔር ዶ/ር ዐቢይን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ላካቸው ብዬ አምናለሁ።


2. የሁለቱም ተልእኮ ሕዝብን ነጻ ማውጣት


የሙሴ ተልእኮ የእስራኤልን ሕዝብ ከተናቁበትና ከተዋረዱበት ከግብጽ ምድር አውጥቶ ወደ ተስፋይቱ ምድር ወደ ከነዓን መምራት ነበር። የዶ/ር ዐብይ ተልእኮስ? እኔ እንደማምነው ዶ/ር ዐቢይ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከጥላቻ፥ ከዘረኝነት፥ ከመከፋፈልና ከመበታተን ነጻ ማውጣት ነው።

እኛ ኢትዮጵያውያን ከተባበርናቸው አገራችንን ከማይምነት፥ ከድህነት፥ ጠባብና ኋላ ቀር ከሆኑ አስተሳሰቦችና አመለካከቶች፥ ከስደትና በዓለም ሕዝቦች ዘንድ ካለን ነቀፌታ ነጻ ያወጣሉ ብዬ አምናለሁ። ይህንንም ለማድረግ እግዚአብሔር ይርዳቸው።


ኢትዮጵያ እጅግ ባለጠጋ አገር ናት። እስከዛሬ ያጣችው ግን በራእይ፥ በብቃትና በመሰጠት የሚመሯትን መሪዎች ነው። ዶ/ር ዐቢይና አብሯቸው የሚመሩን መሪዎች የአገራችንን የትምህርት ጥራት ለማሻሻል ቅድሚያ ከሰጡ፥ ሙስናንና ግፍን ከምድራችን ካስወገዱልን፥ የሕግን የባላይነት በሁሉ ሥፍራ ካሰፈኑ፥ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ሕዝብን በማስቀደም ከመሩን፥ እኛም ደግሞ የምንሠራውን ሁሉ በዕቅድና በጥራት ከሠራን፥ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ፥ ምናልባትም ከአሥር እስከ ሃያ ዓመታት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች መካከል ልትመደብ ትችላለች ብዬ አምናለሁ።


3. ሁለቱም መሪዎች ትሑታን ናቸው


የሙሴ ትልቁ የአመራር ጉልበት ትሕትናው ነበር። ያን በጣም ዓመጸኛና አስቸጋሪ የነበረውን የእስራኤልን ሕዝብ በምድረ በዳ ለአርባ ዓመታት ለመምራት አቅም የሆነለት ትሕትናው ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ የሙሴን ትሕትና እንዲህ ሲል ይመሰክራል፦ “ሙሴም በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ነበር።” (ዘኁልቁ 12፡3)

ትሁት ሰው ከራሱ ይልቅ ሌላውን ያስቀድማል። ሌሎች በእርሱ ትከሻ ቆመው ከሩቅ እንዲታዩ ያደርጋል። በሰው ውስጥ ያለው የተፈጥሮም ሆነ በትምህርትና በልምድ የሚገኘው እምቅ ኃይል ለምልሞና አድጎ ፍሬ እንዲያፈራ ሁኔታዎችን ያመቻቻል። ትሑት ሰው ሌሎች ከእርሱ የተሻለ ሥራ ሲሠሩ ደስ ይለዋል፥ የሌሎችንም ሸክም በመሸከም ያሳርፋቸዋል።


የሙሴን የትሕትናውን ልክ ለመረዳት አንድ ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገውን ምልልስ መመልከት በቂ ነው። የእስራኤል ሕዝብ የወርቅ አማልክት ሠርቶ እግዚአብሔርን ባሳዘነና እግዚአብሔርም ተቆጥቶ ሊያጠፋቸው በተነሳ ጊዜ “አሁን ይህን ኃጢአታቸውን ይቅር በላቸው፤ ያለዚያ ግን ከጻፍኸው መጽሐፍህ እባክህ ደምስሰኝ” በማለት ሙሴ ራሱን ለሌሎች አሳልፎ ሰጠ።


በተመሳሳይ ሁኔታም ዶ/ር ዐቢይ በመስቀል አደባባይ በተፈጸመው የቦንብ ጥቃት ጉዳት ለደረሰባቸው ደም ሲለግሱ፥ ሆስፒታል ሄደው ሲጎበኙአቸው፥ ጌታ ኢየሱስ የደቀ መዛሙርቱን እግር ለማጠብ ከማዕድ እንደተነሳ እርሳቸውም ኤርትራ በተደረገላቸው የክብር ግብዣ አምባሻ ሲያድሉ፥ አሁን ከፍተኛ መሪ ነኝ በማለት ራሳቸውን ከተራው ሕዝብ ሳያገሉ ነገር ግን ከሕዝብ ጋር ሲቀላቀሉ አይተናቸዋል። እነዚህን የትሑት መሪ ባሕርያትን በዶ/ር ዐቢይ ሕይወት ሳይ በኢትዮጵያ አመራር አዲስ ምዕራፍ እየተከፈተ መሆኑን እገነዘባለሁ። እርሳቸውም ይህን ትሕትና እስከ መጨረሻው እንዲጠብቁ እግዚአብሔር ይርዳቸው እላለሁኝ።


4. ከውስጥና ከውጭ የተነሱ ተግዳሮቶችን ማሸነፍ


ሙሴ ለአርባ ዓመታት ሕዝቡን ሲመራ እጅግ ብዙ የውስጥና የውጭ ተግዳሮቶች ገጥመውታል። ከግብጽ ከመውጣታቸው በፊት ፈሪዖን ተገዳድሮታል። ከግብጽ ከወጡ በኋላም የፈሪዖን ሠራዊት ሊያጠፋቸው እስከ ቀይ ባሕር አሳዷቸዋል። የእስራኤል ሕዝብ በምድረ በዳ በሙሴ ላይ በተደጋጋሚ አምጸዋል፥ አመራሩንም በመቃወም ወደ ግብጽ ብንመለስ ይሻላል ብለዋል፤ በእግዚአብሔር ላይ በማመጽ የጥጃን ምስል ሠርተው ሰግደዋል፥ የራሱ ወንድምና እህት እንኳን “መሪ አንተ ብቻ ነህን?” በማለት ተቃውመውታል። በዚህ ሁሉ ተግዳሮት ውስጥ ግን ሙሴ በእግዚአብሔር ኃይልና ጥበብ በመደገፍ በዓላማው ጸና። እግዚአብሔርም ከሁሉ አዳነው።

በተመሳሳይ ሁኔታም ዶ/ር ዐቢይ አመራራቸውን ከጀመሩ ወዲህ የመግደል ሙከራ ተደርጎባቸዋል፥ በተለያዩ ስፍራዎች ሕዝብን ከሕዝብ ጋር እያጋጩ ገና ሥራቸውን ሳይጀምሩ ተስፋ ለማስቆረጥ ጥረት የሚያደርጉ ሰዎች ተነስተዋል። ከዚህም በኋላ የውስጥና የውጭ ተግዳሮቶች ሊነሱ ይችላሉ። ነገር ግን ሙሴን የጠበቀው የእስራኤል አምላክ ዶ/ር ዐቢይንም የተሰጣቸውን ሥራ እስከሚፈጽሙ ድረስ ይጠብቃቸዋል ብዬ አምናለሁ።

ተግዳሮት አስቸጋሪና ዋጋ የሚያስከፍል ቢሆንም በሕይወት የመኖርና የእድገት አንዱ አካል ነው። ተግዳሮት ሲኖር አብዝተን እንጸልያለን፥ በእግዚአብሔር ላይ እንደገፋለን፥ የበለጠ ጥበበኞች እንሆናለን። ሁላችን በአንድነት በመቆም፥ ዕርቅንና ፍቅርን በያለንበት በመስበክ፥ ባልንጀራችንን እንደ ራሳችን በመውደድ፥ ከእኔ ብሔር ይልቅ አገር ይቀድማል፥ ከእኔ ሕይወት ይልቅ ትውልድ ይበልጣል በማለት ዶ/ር ዐቢይን፥ አብራዋቸው ያሉትን ሁሉ እና የኢትዮጵያን ልማት ልንደግፍ ያስፈልጋል። እኛ ሁላችን አንድ ከሆንን የማናሸንፈው ተግዳሮት አይኖርም።


5. ተመሳሳይ ራእይ ያላቸውን መስማት


አንድ ጊዜ ሙሴ የተስፋይቱን ምድር እንዲሰልሉ 12 ሰላዮችን ላከ። ከአሥራ ሁለቱ መካከል ምድሪቱን መውረስ እንችላለንና ወደፊት እንጓዝ ሲሉ አሥሩ ግን መውረስ አንችልም በማለት ሕዝቡ ሙሴን እንዳይከተል ከፍተኛ ቅስቀሳ አደረጉ። በዚያን ጊዜ ሙሴ የሰማው የብዙሃኑን ድምጽ ሳይሆን የሁለቱን ሰዎች ድምጽ ነበር።


ዛሬ ዶ/ር ዐቢይ ያኔ ሙሴ ከነበረው የተሻለ ዕድል አላቸው። ጥቂት ሳይሆኑ ብዙ ኢትዮጵያውያን አብረዋቸው አሉ። ቢሆንም ግን ዶ/ር ዐቢይ ቅድሚያ ሰጥተው ተመሳሳይ ራእይ ያላቸውን ሰዎች በምድራችን የማብዛት ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል። በሙሴ አመራር ተደጋግሞ የታየው ድካም ሥራውን ሁሉ እርሱ ለመሥራት መሞከሩ ነበር። በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር ራእይህን የሚጋሩ ብዙ መሪዎች ያስፈልጉሃል በማለት ሙሴን የሚሰሙና በሙሴ መንፈስ የሚሠሩ ብዙ ተጨማሪ መሪዎችን አስነሳለት።


አሁን ዶ/ር ዐቢይ በሚያስተምሩት በኢትዮጵያ አንድነትና ልማት ራዕይ ጋር ስምምነት የሌላቸውን ሰዎች እንዲሁ በይቅርታና በፍቅር ስም ሥልጣን መስጠት ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላልና ለሰዎች ሹመት ሲሰጥ ጥንቃቄ ማድረግ መልካም ይመስለኛል።


በመጨረሻም በሦስት እና በአራት ወራት ከታዘብኳቸው ነገሮች በመነሳት በኢትዮጵያዊው ዶ/ር ዐቢይና በእስራኤላዊው ሙሴ መካከል ተመሳሳይነት እንዳለ ተመልክቼአለሁ። ሁለቱም መሪዎች በድንገት ለከፍተኛ አመራር በእግዚአብሔር የተጠሩ፥ በጭቆና ውስጥ የነበረውን ሕዝብ ወደ ነጻነት ለመምራት የተላኩ፥ ትሕትናቸው የተመሰከረላቸው፥ ብዙ ተግዳሮቶችን በትዕግሥት ያሸነፉ፥ አይቻልም የሚለውን የብዙሃንን ድምጽ ሳይሆን ይቻላል የሚሉ የጥቂቶችን ድምጽ እየሰሙ በዓላማቸው የጸኑ ናቸው።


በተጨማሪም የተጀመረው የፍቅር፥ የሰላምና የእድገት ራእይ ከግቡ እንዲደርስ ዶ/ር ዐቢይና መንግሥታቸው ቅድሚያ ሰጥተው መሥራት ከሚጠበቅባቸው ነገሮች መካከል አንዱ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ውስጥ መሻሻል የሚገባቸውን ነገሮች ማሻሻልና የሕግን የበላይነት ማስፈን ነው። ለምሳሌ ያህል የገዢው መደብ በተቀየረ ጊዜ ሁሉ የኢትዮጵያ ባንዲራና ብሔራዊ መዝሙር የሚቀየር ከሆነ አገር መታወቂያና መሰረት የላትም ማለት ነው። ኢትዮጵያ ከግለሰቦችና ከፖለቲካ ፓርቲ በላይ መሆኗን ሕገ መንግሥታችን ሊያረጋግጥ ይገባል።


እኛ ደግሞ የትውልዳችን ሙሴ እንደ ብሉይ ኪዳኑ ሙሴ እንዲመራ፥ ዘረኝነትንና መከፋፈልን እምቢ በማለት፥ የምንሠራቸውን ሥራዎች ሁሉ በፍጹም መሰጠትና ታማኝነት በመሥራት፥ የበኩላችንን ድጋፍ ልናደርግ ይገባል። በሚቀጥለው እስከምንገናኝ እግዚአብሔር ሰላሙን ይስጠን።

386 views0 comments